ከሸዋ እስከ ዓድዋ ወደ ገቢ ምንጭነት ያልተሸጋገሩ የቱሪዝም መዳረሻዎች
 ከሸዋ እስከ ዓድዋ ወደ ገቢ ምንጭነት ያልተሸጋገሩ የቱሪዝም መዳረሻዎች


ነአምን አሸናፊ
የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነትና እምቢ ባይነት ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው የዓድዋ ድል የተፈጸመው ከ123 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በወቅቱ የጣሊያን ጦር ብዙም አልሠለጠነችም የሚላት ኢትዮጵያን በመውረር የቅኝ ግዛቱ አካል ለማድረግ ሲያልም በቀላሉ እንደሚያሸንፍና አገሪቱንም ለማስተዳደር ብዙም እንደማያስቸግረው በማሰብ ነበር፡፡
ነገር ግን በወቅቱ የአገሪቱ ሉዓላዊ ግዛት መደፈር ያንገበገባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወራሪውን ኃይል ለመመከትና የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማጠናከር ቆርጠው በመነሳታቸው ህልመኛው የጣሊያን ሠራዊት አንድ ቀን ብቻ በወሰደ የአልሸነፍ ባይነትና በአልበገሬነት በተደረገ ውጊያ፣ ዓድዋ ላይ ድል ተነስቶ ህልሙ መና ሆኖ መቅረቱን የታሪክ ድርሳናት ለዘለዓለም ሲያወሱት የሚኖር የታሪክ ሀቅ ነው፡፡
ድሉን ተከትሎ ‹‹ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ ይችላሉ›› የሚለው አስተሳሰብ ሥር ሰድዶ በአፍሪካ፣ በእስያ፣ እንዲሁም በላቲን አሜሪካ የሚኖሩ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸውና ለማንነታቸው፣ እንዲሁም ለአገራቸው ክብር ለመታገል እንዲነሳሱ ማድረግ ያስቻለ፣ የነፃነትን ችቦ ከፍ አድርጎ የለኮሰ ታሪካዊ ድል ነው፡፡
የዚህን ታሪካዊ የጥቁር ሕዝቦች ድል የተመዘገበበት 123ኛ ዓመት (የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም.) ክብረ በዓልን ለመዘከር በባህልና ቱሪዝም አጋፋሪነት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ጋዜጠኞች ‹‹ከሸዋ እስከ ዓድዋ›› በሚል መሪ ቃል ይህንን ታሪካዊ ጦርነትና ድል ለመከወን የተዘመተባቸውን የተለያዩ ሥፍራዎች በመጎብኘት ወደ ታሪካዊቷ ዓድዋ ከተማ ደርሰዋል፡፡
በጉዞውም ወቅት ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ የትውልድ መንደር እስከ ጦርነቱ እስከተካሄደበትና ድሉ ወደተበሰረባት ዓድዋ ከተማ ድረስ ያሉ ሥፍራዎችን ለመጎብኘት ተችሏል፡፡ በዚህ ጽሑፍም የጉዞውን መዳረሻዎች በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡
ደብረ ብርሃን፣ አንጎለላና አንኮበር
ጉዞው የመጀመርያ መዳረሻ የነበረችው ከደብረ ብርሃን ከተማ ወጣ ብላ የምትገኘውንና የአፄ ምኒልክ የትውልድ ሥፍራ የሆነችውን አንጎለላ ቀበሌን በመቃኘት ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ በዚሁ ቀበሌ ‹‹ኮሶ እንቁላል›› በተባለ ሥፍራ የተወለዱ ሲሆን፣ የጉብኝቱ ቡድንም ይህንን ሥፍራ ተመልክቷል፡፡
በዚህ ሥፍራ የአፄ ምኒልክ እናት ቤት ነበር በተባለ ሥፍራ ላይ አንድ ጠበብ ያለ በአጥር የታጠረ ቦታ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚሁ አጥር ውስጥም ‹‹የአፄ ምኒልክ እትብት የተቀበረበት ሥፍራ›› የሚል ጽሑፍ ይገኝበታል፡፡
ምንም እንኳን አፄ ምኒልክ በዚሁ ቦታ መወለዳቸው በተለያዩ የታሪክ ጸሐፊያንና ድርሳናት ተመዝግቦ የሚገኝ ቢሆንም፣ እትብታቸው የተቀበረበት ሥፍራን በእርግጠኝነት ለይቶ ይህ ነው ማለት በምን ሳይንሳዊ ማስረጃ ተደግፎ ነው የተረጋገጠው የሚያሰኝ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የተወሰኑ ጋዜጠኞችም ይህን ጥያቄ ሲያነሱ ነበር፡፡
የአፄ ምኒልክ ‹‹እትብት ተቀበረበት›› የሚባለው ሥፍራ በተለያዩ መንገዶች ማረጋገጥ ከተቻለ እሰየው፣ ነገር ግን ታሪክን ከአፈ ታሪክ እየቀላቀሉ ማቅረብ የታሪኩን ዋጋ ማሳነስ፣ እንዲሁም ደግሞ አሁን ላለንበት የታሪክ ሽሚያና መቆራቆስ ሊዳርግ ስለሚችል እንዲህ ያሉ ነገሮች በባለሙያ ተጠንተው ብያኔ ቢያገኙ መልካም እንደሆነ ሲገልጹ የነበሩ በርቶች ናቸው፡፡
በመቀጠል ከደብረ ብርሃን ወደ ቀኝ በመታጠፍ 42 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ወደምትገኘው ጥንታዊቷ የአንኮበር ከተማ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን፣ በጉብኝቱ ወቅትም አንኮበር መሠረታዊ የሚባሉ የመሠረተ ልማት አውታሮች እንዳልተገነቡላት መታዘብ ይቻላል፡፡ ከዓመታት በፊት እንደሚሠራ የተወራለት መንገዱም ያለ ምንም ግንባታ የሚገኝ ሲሆን፣ ሥፍራውን ለመጎብኘት በሚደረገው ጉዞ እያንዳንዱ ተጓዥ አቧራ መቃሙና መታጠኑ የግድ ነው፡፡
ይህን ታሪካዊ ሥፍራ ለመንከባከብም ሆነ ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተሠራ ሥራ መመልከት አስቸጋሪ ሲሆን፣ ሥፍራው አሁንም ቢሆን በምኒልክ ዘመን ከነበረበት ይዞታ እምብዛም የተለየ አይመስልም፡፡ ምናልባት የሳር ክዳን ቤቶች ወደ ቆርቆሮ ከመቀየር ባለፈ ይህ ነው የሚያሰኝ የመሠረተ ልማትም ሆነ ሌሎች ተያያዥ የልማት ዕድገቶች አሁንም ብርቅ ናቸው፡፡
ወረኢሉ
ወደ ታሪካዊቷ ወረኢሉ ከተማ የተደረገው ጉዞና ጉብኝት አብዛኛውን የጉብኝት አካል ያሳዘነ ነው፡፡ በወረኢሉ የሚገኘው ስትራቴጂካዊ ሥፍራ ላይ የሚገኘው የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት አብዛኛው ክፍል የፈራረሰ ሲሆን፣ የቀሩት ሁለት ክፍሎች ደግሞ ለመንግሥታዊ አገልግሎት የሚሆኑ ቢሮዎች መጠቀሚያነት ውሏል፡፡
በዚሁ ወረኢሉ ላይ ‹‹አባ ግንባሮ›› በመባል የሚጠራው ልዩ ቦታ ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸውን አንፀው ይኖሩ እንደነበር የታሪክ መዛግብት የሚያስረዱ ሲሆን፣ የጣሊያንን ወራሪ ጦር ለመመከት የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ እንዲሰባሰብበት በክተት አዋጅ አስነግረውታል፡፡
‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፣ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም በእግዚአብሔር ችርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡ ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷልና እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውንም መድከም ዓይቼ እስካሁን ዝም ብለው፣ ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀድም የበደልኩህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህና ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ዕርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልተውህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ፤›› በማለት የክተት አዋጅ የታወጀበት ይህ ታሪካዊ ሥፍራም፣ እንደ አንኮበር ሁሉ የመሠረተ ልማት እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ይታይበታል፡፡
ምንም እንኳን የአንኮበርን ያህል ባይሆንም ይህም ሥፍራ እንኳን የውጭ ጎብኚዎች ስቦ የቱሪስት መዳረሻና የገቢ ምንጭ ሊሆን ቀርቶ ድሉ ያገባናል፣ የእኛም ነው በሚል መንፈስ የተጓዘው የጋዜጠኞች ቡድንንም ቢሆን የፈተነና አስቸጋሪ ነበር፡፡
ይህ ሥፍራ ከአንኮበሩ በተለየ ከመፍረስ የተረፈው ቤተ መንግሥት ወደ መንግሥት ቢሮነት መቀየሩ ነው፡፡ በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የወረዳው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤትና የወረኢሉ ወረዳ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት የሚገኙ ሲሆን፣ ከመፍረስ የተረፈውን ሕንፃ የወረዳው የፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ አንደኛው ደግሞ የቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡
ከተረፉት አንደኛው ሕንፃ የወረዳው ግዥና ንብረት አስተዳደር የሥራ ሒደት ንብረት ኦፊሰር የሚል ጽሑፍ በሩ ላይ የተለጠፈ ሲሆን፣ እንዲያው ካልጠፋ ቦታ ይህን ሥፍራ ወደ ተራ ቢሮነት መቀየሩ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ ለምን ይህ ሆነ? ለሚለውም አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጥ አካል አልተገኘም፡፡ የሚመለከተው አካልም አስፈላጊውን ምልከታ አድርጎ፣ ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ ቢያደርጉለት የገቢ ምንጭ በመሆን ሊያገለግል ይችላል፡፡ አሁን ባለው አያያዝ ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ እዚህ ጋር የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸው ነበር ወደሚለው የነበር ትርክት መገባቱ አያጠራጥርም፡፡
ይስማ ንጉሥ (ውጫሌ)
የውጫሌ ውል የተፈረመበት ሥፍራ ይስማ ንጉሥም ተመሳሳይ የመንገድና ተያያዥ የመሠረተ ልማት ያልተሟሉለት ሲሆን፣ በሥፍራው እየተገነባ ያለው ሙዚየም ግንባታ 50 በመቶ ያህል መድረሱ መልካም ቢሆንም በሥፍራው የሆቴል፣ የመንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘውን ሙዚየም ግንጥል ጌጥ የሚያደርገው ነው፡፡
ሌላው በዚህ ሥፍራ ማስተዋል የሚቻለው ነገር ቢኖር አፄ ምኒልክ የውጫሌ ውልን ሲዋዋሉ የተቀመጡበት ድንጋይ በሚል አንድ ተለቅ ያለ ድንጋይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህ ትርክት ግን አፄ ምኒልክን ከማኮሰስ ያለፈ ምንም ዓይነት ፋይዳ እንደሌለው በርካቶች ሲገልጹ ነበር፡፡
አፄ ምኒልክ ዙፋን ላይ ተቀምጠው የሚያሳዩ በርካታ ፎቶግራፎች በተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት ላይ የሚገኙ ከመሆኑ አንፃር፣ አፄ ምኒልክ የውጫሌ ውልን የተፈራረሙት ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለው ነው የሚለው ትርክት የምዕራባውያን ለኢትዮጵያውያን ከነበራቸው አተያይ የሚመነጭ (ኢሮሴንትሪክ) ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለተመልካች የሚቀርቡ ታሪካዊ ኩነቶችና ሥፍራዎችን በአግባቡ መግለጽ አስፈላጊነትንም ብዙዎቹ አስምረውበታል፡፡
ዓድዋ
ታሪካዊቷ የዓድዋ ከተማን ለመጀመርያ ጊዜ የሚጎበኝ ማንኛውም ጎብኚ በከተማዋ ሁኔታ ግራ መጋባቱ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ በተለይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ስለዓድዋ ያዳመጠ፣ የተመለከተም ሆነ ያነበበ በከተማዋ ከተከናወነው ታሪካዊ ድል በመነሳት ከተማዋ በርካታ የሚጎበኙ ሥፍራዎች እንደሚኖራት መገመቱ ስህተት መሆኑን የሚረዳው ዓድዋ ከተማ ላይ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡
እነዚያ የጣሊያንን ወራሪ ጦር አይቀጡ ቅጣት ሲቀጣ የታዘቡ ተራራዎች ከተራራነት ባለፈ በዙሪያው የጦርነት ውሎውን የሚዘግቡና የሚያስረዱ ምንም ዓይነት ምልክቶች የሉም፡፡ በሥፍራው የነበረው የጋዜጠኞች ቡድን አንድ ላይ በመሆኑና አብረውትም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባልደረቦች በሥፍራው በመኖራቸው ተራራዎቹንና የተካሄደባቸውን ጦርነት አስመልክቶ ገለጻ በማግኘቱ አንደኛውን ተራራ ከሌላኛው መለየት ቢችልም ዓድዋን ልጎብኝ ብሎ የተጓዘ ጎብኚ ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት እጅግ ፈታኝ እንደሚሆኑበት መታዘብ ይቻላል፡፡
ከጉዞ ባለፈ
የዓድዋ ድልን ይሁን ሌሎች ታሪካዊ ኩነቶችን ለመዘከር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በየዓመቱ የተለያዩ ጉዞዎችን በማዘጋጀት ሥፍራዎቹ ያላቸውን ጠቀሜታ ለሕዝብ ለማስተዋወቅና ለማድረስ እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡ ሆኖም ግን በየዓመቱ ከሚደረጉት ጉዞዎችና መዘክሮች ባለፈ እያንዳንዱን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ኩነቶችን በዘለቄታው መንከባከብና ለመላው ዓለም ታዳሚ ለማቅረብ መትጋት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው፡፡
በዚህ ‹‹ከሸዋ እስከ ዓድዋ›› በሚል በተሰኘው የጉዞ መስመር ላይ በርካታ ታሪካዊ ሥፍራዎች ይህ ነው የማይባል የመሠረተ ልማት፣ እንዲሁም የቱሪዝም ትልም ሳይበጅላቸው እንዲሁ ‹‹ታሪካዊ ሥፍራ›› የሚል ስያሜን ብቻ እንደያዙ መታዘብ ይቻላል፡፡
በተለይ የዓድዋ ድልን አስመልክቶ ድሉ ከኢትጵያውያን አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝብ ድል ከመሆኑና በርካቶችን ለነፃነታቸው እንዲነሱ ፈር የቀደደ ከመሆኑ አንፃር፣ በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ከመሆኑ አንፃር በየዓመቱ ከመዘከርና በዓመት አንዴ በሚመጣ በዓል ሰሞን ብቻ ስለጉዳዩ ከማውራት ባለፈ ዓመቱን ሙሉ የሚወሳና የሚጎበኝ ሥፍራ በማድረግ ገቢ ማግኘት የሚቻል ከመሆኑም በላይ አሁን ላለንበት የማንነት ፖለቲካ አቅጣጫ የሚያስይዝና የአንድነትን ጠቀሜታ የሚያስረዳ ህያው ምስክር መሆን ይችላል፡፡