የኢትዮጵያና ኢንዶኔዢያ ወጣቶች የባሕልና የልምድ ልውውጥ አካሄዱ
ቅዳሜ ፣ ታህሳስ 14 ቀን 2019
የኢትዮጵያና ኢንዶኔዢያ ወጣቶች የባሕልና የልምድ ልውውጥ አካሄዱ

የኢትዮጵያና ኢንዶኔዢያ ወጣቶች የባሕልና የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄደ ።
ወጣቶቹ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ በሚገኘው የኢንዶኔዢያ ኤምባሲ ባካሄዱት የባህልና የልምድ ልውውጥ መድረክ የአገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በመድረኩ የአፍሪካ ወጣቶች የሠላም መልዕክት የተሰኘ ኢኒሼቲቭ ይፋ ሲደረግ “የወጣቶችን ድምጽ እናድምጥ” በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮ-ኢንዶኖዥያ ወጣቶች የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል። በኢንዶኔዢያ ኤምባሲ አስተባባሪነት የአፍሪካ ወጣቶች የሠላም መልዕክት የተዘጋጀ ሲሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር በሁሉም የአፍሪካ አገራት ከሚገኙ የወጣቶች ማኅበራት ጋር እየዞረ የሠላም መልዕክት የሚሰበስብ ይሆናል። መልዕክቱ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ከ50 የሚበልጡ የአፍሪካ አገራትን በማደረስ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳል። በዚሀም ወጣቶቹ ለዓለም ሠላም አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ተብሏል። በመድረኩ የተገኙት የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት ወጣቶች የአገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር የጀመሩትን እንቅስቃሴ አድንቀዋል። መድረኩ የሁለቱን አገራት ሕዝቦች የባሕል ልውውጥና የሁለትዮሽ ግንኙነቱም ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል። የኢንዶኔዢያ አምባሳደር አልቡሽራ ባንሱር ለሁለቱ አገራት ግንኙነትና ለወጣቶች ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። አምባሳደር አልቡሽራ ባንሱርም ዝግጅቱ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን እንደሚያጠናክርና ወጣቶቹም አገራቱ በትብብር እንዲሰሩ በማድረግ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና ፀሃፊ ወጣት ኤርሚያስ ማቲዎስ በበኩሉ በሁለቱ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት መኖሩንና ይህን ወጣት ኃይል ለአገራቱ የጋራ ልማት መጠቀም እንደሚቻል አንስቷል። በባህልና ልምድ ልውውጥ መድረኩ 200 ወጣቶችና የሁለቱ አገራት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ምንጭ ኢዜአ